ከአቤቱታ ሮሮ እና ብሶት ተላቆ ተጨባጭ ስራ መስራት ያለበት ጊዜ ላይ መሆናችንን እንወቅ:: —

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)​ — ገባንም አልገባንም መጻፋችንን መመካከራችንን አናቋርጥም::ዋናው ጉዳያችን ወያኔን ገንድሶ መጣል ላይ መሆኑ መዘንጋት የለብንም::ካሁን በፊት የተሰሩ ስራዎችን መከለስ እና እንዳላዋጡ ማመንም ግድ ይላል::ተጨባጭ ስራ መስራት ሲገባ በስድብ አሉባልታ አቤቱታ ሮሮ እና ብሶት ላይ ስንዘፍን ኖረን አሁንም ባለንበት እየረገጥን ነው::በተደጋጋሚ እንደሚነገረው የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ነን::ወያኔማ አጀንዳም ፈጥሮ ይሁን ሃይል ተጠቅሞ ስራውን እየሰራ ነው::እኛ ደሞ ወያኔ በሚሰጠን አጀንዳ እየተለባለብን በሚጠቀመው ሃይል የሚፈጠረውን አቤቱታ እና ብሶት እያወራን ተጨባጭ ስራ ሳይሰራ በወሬ ናዳ ተከበን በሌሎች ትከሻ ነጻ ለመውጣት እንውተረተራለን::

በመሐል አገር እና በዳር አገር ለሃገር እና ሕዝብ ነጻነት የሚታገሉ የለውጥ ሃይሎችን ስራዎች ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ውጥተው ተጨባጭ ስራዎች ላይ እንዲተከሉ እያንዳንዳችን እንደ ዜጋ የመተባበር አብሮ የመንቀሳቀስ ግዴታ አለብን::ነጻነት ያለው በያንዳንዳችን እጅ ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም::ወያኔ በለውጥ ሃይሎች መካከል መተማመን እንዳይኖር ጠንክሮ እየሰራ ሲሆን ፖለቲካ ያልገባቸው የመኖሪያ ፈቃድ ፈላጊዎችም በአውሮፓ ተቀምጠው ሳያውቁ በስሜት እና በደመነብስ በሚረጩት መርዝ በለውጥ ሃይሎች መካከል ጠንካራ የሆነ የትብብር ስራ እንዳይሰራ ጋሬጣ ከመሆን አልፈው ለወያኔ የስልጣን እድሜ ሚናቸውን ያበረክታሉ:: ነጻነት በማህበራዊ ድህረገጽ የሚገኝ የሚመስላቸው በጻፉ ቁጥር ሁሉ ወያኔ የወደቀ የሚመስላቸው እና እፎይ ብለው የሚተኙ ሁሉ የትግል ስራዎችን በተጨባጭ እንዲሰሩ ራሳቸውን መከለስ ያለባቸው ደረጃ ላይ መድረሳችንን ሊያውቁት ይገባል::ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል::ለውጡ ግን በሁሉም የለውጥ ሃይሎች ጎን ለጎን በመቆም እና ተግባራዊ ስራዎች በመስራት እንጂ ሮሮ እና ብሶት ካለተጨባጭ ስራ እና መፍትሄ በመተንፈስ አይደለም::

ወያኔ በፖለቲካ ስራዎች በልጦናል::ይህንን ማመን ግድ ይላል::ካለፈው ስህተት ያልተማረ ካለፈው ስህተት የማያገግም እና ስህተቱን ሸፍኖ የሚሄድ ሌላ ትልቅ ስህተት እንደሚሰራ በጊዜ ሊያውቅ ይገባል::በለውጥ ሃይሎች መካክል – ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አለመኖሩ + በጥርጣሬ መተያየቱ + በሃሜት ስድብ እና አሉባልታ መወጠሩ + ለግል ጥቅም ጉዳይ እና ለመኖሪያ ፈቃድ ፖለቲካን መያዙ + የአንድ ሰሞን የሆይሆይታ እና ወረት ፖለቲካ + ራስን በባዶ ማግዘፍ ፕሮፓጋንዳ + ግትርነት + ከኔ በላይ አዋቂ ላሳር + የአጀንዳ ክንብንቦሹ የመሳሰሉት ጉዳዮች ተጨባጭ ስራዎች እንዳይሰሩ በዘር እና በቋንቋ እንድንከፋፈል እንዲሁም በውስጥ መደብ እና ባልበሰሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮች የጎንዮችሽ ሽሙጥ እንድንተያይ አድርጎናል:: አናምንም ብለን እንኮፈሳለን እንጂ እስካሁን በታዩ ሂደቶች ከፕሮፓጋንዳ ውጪ በተግባር የታየ አንድም ነገር የለም:: በጋራ እንቁም::በአንድነት እየተሰሩ ባሉት የትግል ጅማሮዎች ላይ እንረባረብ::ነጻነታችንን የምናገኘው በሌላው መስእዋትነት ሳይሆን በራሳችን መስእዋትነት እንደሆነ አንዘንጋ::ከአቤቱታ ሮሮ እና ብሶት ተላቆ ተጨባጭ ስራ መስራት ያለበት ጊዜ ላይ መሆናችንን እንወቅ:: #ምንሊክሳልሳዊ

Leave a Reply