Friday, 11 September 2015 09:22
ማህሌት ኪ/ወልድ እና አለማየሁ አንበሴ
  • “የበግና የበሬ ዋጋ ብዙ ጭማሪ አላሳየም”
በዘንድሮ የአዲስ አመት የበዓል ገበያ፣ የዶሮ ዋጋ ከበፊቱ በእጥፍ የጨመረ ሲሆን የበግና የበሬ ዋጋ ካለፉት በአላት የተሻለ እንደሆነ ነጋዴዎችና ሸማቾች ተናገሩ፡፡
በአቃቂና በሳሪስ አካባቢ ዶሮ ከ200 ብር እስከ 400 ብር የሚሸጥ ሲሆን፤ በግ ከ1100 እስከ 3500 ብር፣ በሬ ከ4500 እስከ 25ሺ ብር፣ ፍየል ከ750 እስከ 4ሺ ብር እየተሸጡ ነው፡፡ በሾላ ገበያ በግ ከ900 ብር እስከ 4500 ብር፣ በሬ ከ5 ሺህ እስከ 22 ሺህ ብር ሲሸጥ፤ የዶሮ ዋጋ ከ180 እስከ 350 ብር  እንደሚደርስ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በካዛንቺስ አካባቢ ደግሞ በግ ከ800 ብር እስከ 3 ሺህ ብር የሚገኝ ሲሆን የዶሮ ዋጋ ከፍተኛው 400 ብር ነው፡፡ በዘንድሮ የበዓል ገበያ ለእርድ ከሚውሉ እንስሳት መካከል የዶሮ ዋጋ ከአምናው በዓል በእጥፍ የጨመረ ሲሆን የበግና የበሬ ዋጋ ግን የተረጋጋ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የበግና የበሬ ነጋዴዎች በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ በቁም እንስሳት አቅርቦት በኩል ችግር እንደሌለ ጠቁመው፣ ከብት አርቢው ዋጋ ለቀቅ በማድረጉ ብዙም ጭማሪ አላደረግንም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በበአሉ ወሳኝ ከሆኑት መካከል በአብዛኞቹ የአዲስ አበባ የገበያ ስፍራዎች ቅቤ በኪሎ እንደየአገሩ ከ140 ጀምሮ እስከ 250 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የቅቤ ገበያም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር እንደየደረጃው በኪሎ ከ30 ብር ጀምሮ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ቀይ ሽንኩረት በአትክልት ተራ ገበያ በችርቻሮ ከ14.50 እስከ 16 ብር በጅምላ ደግሞ ከ13-50 እስከ 14 ብር እንደየአይነቱ እየተሸጠ የሚገኝ ሲሆነ በሾላ ገበያም ከ13 ብር እስከ 14 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
ነጭ ሽንኩረት በተለያዩ የገበያ ቦታዎች በኪሎ ከ60 ብር ጀምሮ እስከ 70 ብር እየተሸጠ ሲሆን፡፡ አይብ በኪሎ ከ40-50 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የአበሻ እንቁላል በአብዛኛው የመዲናችን ገበያዎች 3.30 እስከ 3.75 እየተሸጠ ሲሆን የፈረንጁ ከ3.50 እስከ 3.75 በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply