የማያበራው የፋና ብሮድካስቲንግ ቅጥፈት ……………

በምህረት እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ኡስታዞቻችን እና ወንድሞቻችን በሰሩት ጀብድ ይኮራሉ እንጂ አይፀፀቱም !!! ………………..

አቡ ዳውድ ኡስማን ………………………

ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በድህረገፁ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች እና ፍትህ ሚኒስተር ለ 238 የሚሆኑ እስረኞች ምህረት መደረጉን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 6 የሚሆኑት በኡስታዝ አቡበከር አህመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ውድ ኡስታዞቻችን እና ወንድሞቻችን እንደሚገኙበት ተገልፆል፡፡

ሆኖም ፋና ብሮድካስቲንግ በገለፃው ላይ ምህረት የተደረገላቸው ስድስቱ ሙስሊሞች በሰሩት ስራ በመጸፀታቸው መሆኑን የገለጸ ቢሆንም የፍትህ ሚኒስተር በድህረገፁ ላይ ባሰፈረው መረጃ ላይ ግን ተፀፅተው ምህረት ተደረገላቸው የሚል መረጃ አለቀቀም፡፡

በተደጋጋሚ በኮሚቴዎቻችን ላይ የሐሰት ፕሮፖገንዳ በመንዛት የሚታወቀው ይህ የራዲዬ ጣብያ እስከዘሬ ሲነዛው ለነበረው ፕሮፖጋንዳ ማጠናከሪያ ይሆነው ዘንድም ፍትህ ሚኒስተር አዲስ አመትን በማስመልት ሰጠሁት ያለውን ምህረት ከሌሎች የህግ ታራሚዎች በተለየ መልኩ ኮሚቴዎቻችን እና ወንድሞቻችን ስለተፀፀቱ ምህረት እንደተደረገላቸው አስመስሎ አቅርቧል፡፡ በዚህም የተነሳ ስድስቱ ወንድሞቻችን ይቅርታ ጠይቀው ነው፣ አልጠየቁም የሚል አጀንዳ በሰፊው በማህበረሰቡ ዘንድ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡

ይህን ጉዳይ ባጭሩ ለመመልከት ፍትህ ሚኒስተር ምህረት አደረኩላቸው ያላቸው ስደስቱ ወንድሞቻችን እንዲፈቱ መወሰኑን የሰሙት ሊጠይቃቸው ከሄደው ቤተሰባቸው እና ጠያቂዎቻቸው ነበር፡፡ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደርም ጳጉሜ 6 ለህዝብ በሚዲያ ይፋ ከተደረገ ቡሃላ መስከረም 1 ቀን ሁላቸውንም አንድ በአንድ በተናጠል በመጥራት ፍትህ ሚኒስተር ምህረት ካደረገላቸው እስረኞች መካከል እነሱም እንደሚገኙበት እንደነገራቸው ተገልፆል፡፡ በወቅቱ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ይህን በተናጠል እየጠራ በሚያስታውቅበት ወቅት “ከሌላው ተለይቼ ለምን ለኔ ምህረት ተደረገልህ ትሉኛላችሁ ሌሎች ወንድሞቼስ” የሚል ጥያቄ ኡታዞቻችን እና ወንድሞቻችን ሲያነሱ ነበር፡፡

የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ለዚህ ምህረት እንደምክንያት ያቀረበላቸው በጥፋታችሁ ስለተፀፀታችሁ የሚል ሳይሆን በማረሚያ ቤት ውስጥ ባላቸው ጥሩ ስነምግባር እንደሆነ ብቻ ሲገልፅ ነበር፡፡ በእርግጥ ሁሉም ኮሚቴዎቻችን እና ወንድሞቻችን በማረሚያ ቤቱ እጅግ የሚወደዱ እና በሚያሳዩት ስነ ምግባራቸው አይደለም የማረሚያ ቤቱ ታሳሪዎች ይቅርና የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች እና ሃላፊዎቹም ሳይቀር የሚመሰክሩላቸው ቢሆንም የነዚህ ስድስት ሰዎች መፈታት ምክንያቱ ፖለቲካዊ እንጂ ሃላፊዎቹ እንዳሉት ጥሩ ስነምግባር ማሳየታቸው አይደለም፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ህዝቡ ላይ ለመንዛት የፈለገው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እንዳለ ሆኖ የኢፌዴሪ የይቅርታ ሥነ-ሥርዓት ደንብ መሰረት በህጉ የተቀመጠውን ደንብ በማሟላት ታሳሪዎች በምህረት እንደሚለቀቁ ይደነግጋል፡፡ ይህን ምህረት ለማድረግም በአዋጁ መሰረት የተቋቋመ ቦርድ ያለ ሲሆን ማንኛውም በህጉ መሰረት ይቅርታ የማይደረግለት ወንጀለኛ ካልሆነ በስተቀር የይቅርታ ጥያቄ ሲያቀርብ የይቅርታ ቦርዱ በመሰብሰበው ጉዳዩን ተመልክቶ ይቅርታውን ሊቀበል አልያም ውድቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የተቀበለውን ጉዳይም ለሃገረቱ ፕሬዝደንት በማስፈረም ያፀድቃል፡፡

በ1996 በፀደቀው የኢፌዴሪ የይቅርታ ሥነ-ሥርዓት ደንብ መሰረት(በ 2007 በአዲስ መልኩ ተሻሽሎ ፀድቋል) የአዋጁ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 2 ደግሞ ይቅርታ የጠየቀ እስረኛ ብቻ ሳይሆን ምህረት የሚደረግለት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና የፍትህ ሚኒስተር በጋራ ሆነው ምህረት ሊደረግላች የሚገቡ ታሳሪዎችን በራሳቸው ምርጫ በመምረጥ ለይቅርታ ቦርድ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡

የኡስታዞቻችን እና የወንድሞቻችን ምህረት ተደረገላቸው የተባለውም ፋና ብሮድካስቲንግ እንደዘገበው በሰሩት ስራ ስለተፀፀቱ ሳይሆን የኢፌዴሪ የይቅርታ ሥነ-ሥርዓት ደንብ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ በሰፈረው መሰረት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና የፍትህ ሚኒስተር በጋራ ሆነው ምህረት ሊደረግላች የሚገቡ ታሳሪዎችን በራሳቸው ምርጫ በመምረጥ ለይቅርታ ቦርድ በማቅረብ ምህረት እንዲደግላቸው መደረጉን ፍትህ ሚኒስተር በድህረገፁ ባሰፈረው መረጃ መሰረት መረዳት ይቻላል፡፡

አዲሱን አመት በማስመልከት ለስድስቱ ኡስታዞቻችን እና ወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆን በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ታስረው ለሚገኙ 238 እስረኞች ፣በአማራ ክልል 2 ሺህ 49 እስረኞች፣በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች ክልሎችም የክልሉ ፍትህ ቢሮ በስራቸው በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ታስረው ለሚገኙ እስረኞች አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ በምህረት በርካታ እስረኞችን እንዲፈቱ ማደድረጋቸው ተዘግቧል፡፡

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና የፍትህ ሚኒስተር በጋራ ሆነው ምህረት ሊደረግላች የሚገቡ ታሳሪዎችን በራሳቸው ምርጫ የሚመርጡበት አሰራር ጠቃሚ መሆኑን በፍትህ ሚኒስተር ስር በ 2004 በአቶ ሙሉጌታ አያሌው በተባለ ሰው የተዘገጀው ጥናት አምልክቷል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ካቀረባቸው መካከል
– የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ ለማይችሉ ታራሚዎች ተደራሽ መሆን መቻሉ፣
– የጠራ መረጃ ስለሚሰበሰብ ለቦርድ የውሳኔ ሀሳብ አቀራረብ አመች መሆኑ፣
– በአንድ ጊዜ የብዙ ታራሚዎችን ጉዳይ ማስተናገድ መቻሉ፣
– በጥናቱ ውስጥ ለሚካተቱት ታራሚዎች ይቅርታን አስመልክቶ እና ወደፊት ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ሊከተሉት ስለሚገባ ጉዳይ ትምህርት ለመስጠት አመች ጊዜና ሁኔታ ስለሚፈጥር የሚሉትና የመሣሠሉት ናቸው፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ ተቋሟች ከታራሚዎች መካከል ምህረት ሊደረግላቸው ይገባል በማለት ለይቅርታ ቦርድ 2620 ታራሚዎች ምህረት እንዲደረግላቸው ያደረጉት በ 2004 ነበር፡፡ ከዛ ወዲህ በየአመቱ የዚህ መሰሉ የምህረት አሰጣጥ ቀጥሏል፡፡

በጥናቱ በተቀመጠው መሰረት በዋነኝነት ምህረት የሚደረግበት ምክንያቶች አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ኃይማኖታዊ ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ለፍትህ፣ ለሠላምና ለፀጥታ፣ለሠብዓዊ መብት መከበር እና ወንጀለኛው ለማስተማር/ለማቋቋም/ የሚሉት ናቸው፡፡በአገራችን ኢትዮጵያም እንዳየነው የይቅርታ ዓላማ የህዝቡን ጥቅምና ደህንነት መጠበቅ ሆኖ የህዝቡን ጥቅምና ደህንነት እስከጠበቀ ድረስ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ይቅርታ እየተሰጠ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ማየት እንደሚቻል በጥናቱ ተቀምጧል፡፡

በመሆኑን ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ኡስታዝ ባህሩ ኡመር፣ወንድም ሷቢር ይርጉ፣ወንድም ሙኒር ሁሴን፣ወንድም አቡበከር አለሙ እንዲሁም እስካሁን በውል ያልታወቀው ስድስተኛው ሰው ምህረት ተደርጎላቸው ይፈቱ የተባለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ወይም ፋና ኤፍ ኤም 98.1 በሐሰት እንደዘገበው በሰሩት ስራ ስለተፀጸቱ አልያ ይቅርታ ጠይቀው ሳይሆን ከላይ በተቀመቀጠው ማብራሪያ መሰረት መንግስት በራሱ ሰዓት ምህረት አድርጌላቸው እንዲፈቱ ወሰንኩኝ ማለቱን ሁላችንም ልንረዳው ይገባል፡፡

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስረው የሚገኙት እና በዝዋይ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ኡስታዝ ባህሩ ኡመር የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ ሲያስተላልፍባቸው በደስታ እና በወኔ በሰሩት ስራ እንደማያፍሩ፣ንፁሃን በመሆናቸው የህሊና እረፍት እንደሚሰማቸው በችሎቱ ፊት አላህን እያመሰገኑ ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጥፋታ ተብለውም የቅጣት ማቅለያ አቅርቡ ሲባል ንፁሃን በመሆናቸውን አንድም የቅጣት ማቅለኛአ አናቀርብም ያሻችሁን ፍረዱ በማለት በወኔ እና በቆራጥነት ፖለቲካዊ ውሳኔውን ተቀብለዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኮሚቴዎቻችን ላይ በተደጋጋሚ የሚያሰራጨው የተዛባ መረጃ የሙስሊሙን ማህበረሰብ የመብት ትግል እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ አስመስሎ በማቅረብ ሌላ እምነተ ተከታዬችን ለማስበርገግ እና ህዝቡን ለመከፋፈል መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

በመሆኑም ስለህዝብ የታገሉ፣የሰላምን አስፈላጊነት በአደባባይ የሰበኩ፣ ከሁሉም ሃማኖቶት ተከታዬች ጋር ተከባብሮ መኖርን ያስተማሩ፣ ህግ የጣሰውንም አካል ህግ አክብር ብለው ህግ ጠቅሰው ያሳሰቡ ጀግኖች ፣ ይህን በማድረጋቸውም ታስረው፣ በመገረፋቸው፣ በመሰቃየታቸው እና በመድማታቸው ከአላህ ዘንድ የሚያገኙትን ምንዳ እያሰቡ አኼራቸውን የሚናፍቁ እና የሚደሰቱ ወንዶች እንጂ ኢስላሜን አትንኩብኝ በማለታቸው የሚፀፀቱ ደዩሶች አይደሉም፡፡

ሊፀፀት የሚገባው፣ሊያፍር የሚገባው እውነትን የቀበራት አካል እንጂ ወኪሎቻችን አይደሉም!!

የተቀሩትንም ወኪሎቻችን አላህ በድል የሚፈቱ ያድርጋቸው!!

አሚን !!

Leave a Reply