- ”አቶ ሞላ አስገዶም ሱዳን ውስጥ ወደ አልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል።አብረውት የነበሩት ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ከሰላ ውስጥ ናቸው” ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ
- ”ሞላ ከታጣቂዎቹ ጋር ኢትዮጵያ ገብቷል የሱዳን መንግስትን እናመሰግናለን” ፋና ራድዮ ።
የትግራይ ሕዝብ ንቅናቄ ድርጅት (ትህዴን) ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም ከነበሩበት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ማምለጣቸውን አርብ ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ተዘግቧል።ይህንኑ ዜና መስከረም 2/2008 ዓም የኢህአዴግ/ህወሃት ልሳንነቱ የሚነገርለት ራድዮ ፋና ”ራሱን የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ በማለት የሚጠራው እና በኤርትራ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጦር ክፋይ ትናንት ወደ ሀገሩ ገባ።” በማለት ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን ታዋቂ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ”ሱዳን ትሪቡን” የአቶ ሞላን ማምለጥ እና ኢትዮጵያን፣ሱዳንን እና ኤርትራን በምታዋስነው ሃምዳይት ከተማ አካባቢ ከኤርትራ ወታደሮች ጋር ግጭት እንደነበር እና የሱዳን ወታደሮች ሽፋን ሰጥተው ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለሱዳን ወታደሮች ማስረከባቸውን እና ወደ ሱዳን ከሰላ ግዛት በምትገኘው ዋድ-አል-ሂሉ ከተማ መወሰዳቸውን እና መሪዎቻቸው ወደ አልታወቀ የሱዳን ከተሞች መወሰዳቸውን ጋዜጣው አክሎ ያብራራል።
የአቶ ሞላ መጥፋት በህወሃት ፣ሱዳን እና ሻብያ መሃከል የሚፈጥረው አዲስ የፖለቲካ ትኩሳት
የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ሞላ አስገዶም ሁለት የፖለቲካ ትኩሳቶችን እንደ አዲስ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።እነርሱም በሱዳን እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻከር እና በትግራይ ተወላጆች እና በኤርትራውያን መካከል አዲስ የበቀል ስሜት ሊፈጥር የመቻሉ ድንገት ነው።
በሱዳን እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻከር
በሱዳን እና በኤርትራ መካከል የነበሩ ይቆዩ ግንኙነቶች አንድ ጊዜ ሲሰምር ሌላ ጊዜ ሲደበዝዝ እና እንደ ኳታር ያሉ ሀገሮችን ሸምጋይነት እየጠየቁ ቀጥለዋል።ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ግን የአቶ ኢሳያስ እጅ ደቡብ ሱዳን ውስጥ መገኘት እና ለደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ከህወሃት ተቃራኒ መቆም ሁሉ ሱዳን ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲዋዥቅ አድርጎታል።
ይህ በእንዲህ እያለ ነው እንግዲህ ከኤርትራ አምልጠው ሱዳን ከሰላ ግዛት ገብተው እና በሱዳን ወታደሮች ተደግፈው እንደ ፋና አገላለፅ ኢትዮጵያ ገቡ የተባሉት የአቶ ሞላ ጉዳይ የሳምንቱ መጨረሻ ወሬ የሆነው።ይህ ማለት ሱዳን ቀድሞውንም ከሀወሃት ጋር ተነጋግራ ነበር ማለት ነው? ያልተነጋገረች ቢሆንስ ከኤርትራ እየተፈለገ መሆኑን ያወቀች ግለሰብን ኤርትራ ውስጥ ምን አይነት የፀጥታ ችግር እንደፈጠረ ሳታውቅ ለኢትዮጵያ አሳልፋ ትሰጣለች ማለት ነው?
በእዚህም በኤርትራ ላይ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚስጥር የደረሰችው ስምምነት አለ ማለት ነው? እነኝህ እና ሌሎች ጥያቄዎች በሙሉ በሱዳን እና በኤርትራ ማካከል የነበሩ ግንኙነቶችን የሚያጎድፉ ናቸው።በተለይ ሱዳን ላደረገችው አስተዋፅኦ ምስጋና አቀረበ የተባለው የህወሃት መንግስት በኤርትራ እና ሱዳን መካከል አዲስ ቅራኔ የሚፈጥር ነው።
ይህ ብቻ አይደለም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ አዳዲስ አሰላልፍ የምትፈልገው አሜሪካ ከሱዳን ጋር የሚኖሩ ግጭቶች ለኤርትራ ከአሜሪካን ጋር ግንኙነት ለማደስ ጥረት እያደረገች ነው እየተባለ ሰሞኑን የሚነገረው ዜና አዲስ ኃይል ይጨምራል።ሱዳን እራሷን ከኢትዮጵያም ሆነ ከኤርትራ ወገን ባለመሆን ገለልተኛነትን ለማራመድ ስለሚቸግራት አጣብቂኝ ውስጥ የመግባት እድሏ ትልቅ ነው።በእዚህ ሁሉ መካከል ግን ኤርትራ ውስጥ የመሸጉት የህወሃት ተቃዋሚ ኃይሎች አመቺ የመጠናከርያ ዕድል እንደተከፈተላቸው ለማወቅ ይቻላል።ይሄውም አቶ ኢሳያስ ሙሉ ኃይላቸውን በጸረ-ሱዳን እና ህወሃት መንገዳቸው ከኢትዮጵያ የነፃነት ኃይሎች ጋር በጠነከረ መንገድ እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ነው።
በትግራይ ተወላጆች እና በኤርትራውያን መካከል አዲስ የበቀል ስሜት ሊፈጥር የመቻሉ ድንገት
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
መስከረም 3/2008 (ሴፕቴምበር 14/2015)