ግንቦቶቹ የደምህት አመራርና ወታደሮች ከድተው ለወያኔ እጅ መስጠታቸውን የኤርትራው ትግል እየተጠናከረ ስለሆነ ነው እያሉ ይቀልዱብናል። መቸም የጨነቀው ብዙ ሊል ይችላል ግን ግንቦቶቹ አንድ ነገር እባካችሁ ተረዱ፤ መጀመሪያ የራሳችሁን ግንቦት 7 የሚባለውን ቤታችሁን አጠናክሩ። ለራሳችሁ ጥንካሬና በእግራችሁ ለመቆም ስሩ። ሊቀመንበራችሁም አስመራ ግብቶ ግንቦትን የማጠናከርና ወደ ስራ ማስገባት ሳይሆን የተደራጁ ሌሎች ሃይሎችን ማፍረስ ላይ ነው እየደከመ ያለው። መጀመሪያ የራስን ቤት አጠናክሮ ሃይል ፈጥሮ ነው ሌሎች ጋ ተፅኖ መፍጠርም ማሳመንም የሚቻለው እንጅ የሻቢያን የማስገደድ አቅም ተጠቅማችሁ ዛሬ ውህደት ጥምረት ብትሉ ጊዜያዊ ተስፋ ከመስጠት ያለፈ ነገ ግን ውድቀት ነው። “ጭብጥ ቆሎ ይዘህ ወደ አሻሮ ተጠጋ” የሚባለው ፈሊጥ ትግል ላይ አይሰራም።
በደሚት በኩል ያጋጠመውን ሁኔታ ሁሉም በትምህርትነት መጠቀም ቢቻል ብዙ መማር በተቻለ (መማር የማይችሉትን ሳይጨምር)። ለማንኛውም ሞላ አስገዶም ወደ 700 የሚሆኑ ወታደሮች ከነ ሙሉ ትጥቃቸውና ንብረታቸው ይዞ ለወያኔ እጅ ሰጥቷል። ወደ ወያኔ ሲሻገሩ ደንበር ላይ ከነበረው ከሻቢያ ወታደር ጋር ከባድ ውጊያ አድርገዋል። ከሁለቱም ወገን የሞተም የቆሰለም አለ። 50 የሚሆኑ ሞላን ተከትለው ሊሄዱ የነበሩ በጦርነቱ መሃል በሻቢያ ተይዘዋል። በተፈጠረው ሁኔታ ኤርትራ በቀሩት የደሚት አባላትና ሲከዱ በተያዙት ዘንድ ብዙ መተረማመስና መጥፎ ሁኔታወች እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ብዙ ኢትዮጵያኖች ሊጎዱ እንደሚችሉ ማሰብ አይከብድም።
እኔ እንደሚገባኝ የነ ሞላ ክዳት ከጥምረቱ ጋር የተያያዘ ነው መባሉ የሚረባ ወሬ አይደለም። ከሁለት መሰረታዊ ጉዳይ የሚነሳ ይመስለኛል። አንደኛው ነገር በሻቢያ በኩል ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጭና የምር አለመሆኑን በረጅም ጊዜ የተረዱት ከመሆን የተነሳ ሊሆን ይችላል። ሌላው ነገር እነ ሞላ ከወያኔ ጋር ባላቸው የዘር ግንድ ግንኙነት የተነሳ ለረጅም ጊዜ ትስስር አድርገው ቆይተው አሁን ለመክዳት የተመረጠ ጊዜ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት መውሰድ ይቻላል። ለሁሉም ወያኔን የማስወገዱ ስራ ገና ብዙ ነገር ይጠይቃል። በጠራ አስተሳሰብና በጽናት በሚረጋገጥ የተግባራዊ እንቅስቃሴ እንጅ በንግግር የትም አይደረሰም። መካሪ የሌለው ንጉስ አንድ አመት አይነግስ እንደሚባለው ግንቦቴወች ከባዕዳን ሃይሎች ይልቅ ከኢትዮጵያኖች ምክር ውሰዱ።